Monday 12 November 2012


ኪዳነወልድ ክፍሌ
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ (ከ፲፰፻፷፬ እስከ ፲፱፻፴፯ ..)
የህይወት ታሪክ
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ በ፲፰፻፷፬ .. ተወለዱ። ለትምህርት ሲደርሱ በአካባቢያቸው የነበረውን የአገራቸውን ትምህርት ተማሩ። በኋላም ወደ ጎንደር ተጉዘው የመጻሕፍትን ትርጓሜ አጠኑ። በጊዜው የነበራቸው የቀለም አቀባበል፣ የሚስጥር መመራመርና መራቀቅ በጉባኤው ላይ «የቀለም ቀንድ» የሚል ቅጽል ተሰጣቸው።
አለቃ ኪዳነወልድ ከግዕዝና አማርኛ ሌላ አረብኛ፣ ዕብራይስጥኛ፣ ላቲን፣ ሌሎችንም ቋንቋዎች አጠናቅቀው ያውቁ ነበር። አለቃ ኪዳነወልድ በእየሩሳሌም ለ፳፪ ዓመት ተቀምጠዋል። በዚህም ወቅት ብሉይና ሀዲስ በሦስት ቋንቋ ጠንቅቀው አመሳክረው ተርጉመዋል። ኪዳነወልድ ክፍሌ በ፲፱፻፳፮ .. የመጀመሪያውን መዝገበ ፊደል አውጥተው ከልዩልዩ ቋንቋዎች ጋር በማመሳከር አሳትመዋል። የኢትዮጵያ ፊደል አመጣጡንና ባህሉን በውል አስተባብረው በማቅረባቸውም በጊዜው ተቋቁመው ለነበሩት ትምህርት ቤቶች መመሪያና መማሪያ ለመሆን በቅተዋል። ቀጥለውም ትንሽ አማርኛ ፊደል ከአረብና ከዕብራይስጥ አቆራኝተው አሳትመዋል።
አለቃ ኪዳነወልድ በተለያየ ዘይቤ ያቀርቧቸው የነበሩት ግጥሞች ለትውልድ ታላቅ ጥቅም ይሰጣሉ ተብለው የሚገመቱ ናቸው። እንዲያውም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪቃ የብዙ ሺህ ዘመናት ነፃ አገር ባለፊደልና ባለቋንቋ የሆነች እሷ ብቻ ስለሆነች ትውልድ ያገሩን ትምህርት በመጀመሪያ እንዲማር ያካሂዱት የነበረው ቅስቀሳ በቀላሉ አይታይም። በዓለም ስማቸው የገነነ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ፣ የጽሑፍ ባለአጉዛዎች የሚደነቁባቸው በራሳቸው ቋንቋ ጽፈው ለዓለም የአቀረቧቸው ሥራዎች ናቸው ይላሉ።
አለቃ ኪዳነወልድ ለኢትዮጵያ በአላቸው አቅም በብሔራዊ ስሜት ተነሳስተው ለታሪክ የሚቀርቡ በርከት ያሉ መጻሕፍት ጽፈው አሳትመዋል። በተለይም ከዘጠኝ መቶ ገጾች በላይ የሆነው «የሰዋሰው መጽሐፍ» ታላቅ እንደሆነ ይነገራል። አለቃ ኪዳነወልድ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰው ነበሩ።
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በተወለዱ ፸፪ ዓመት እድሜያቸው፤ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓመተ ምሕረት አርፈው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።

ምንጭ ዊኪፒዲያ




No comments:

Post a Comment